image
image
image
image
image

በልደታ ክ/ከተማ “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ቃል የፓናል ውይይት ተካሄደ

ጥቅምት 4, 2017
በልደታ ክፍለ ከተማ ለ19ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘውን ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን አስመልክቶ የፀጥታ አካላት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የምክር ቤት አባላት እና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የፓናል ውይይት ተካሂዷል። የሰንደቅ ዓላማ ቀንን በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያከበረ የሚገኘው የክፍለ ከተማው አስተዳደር፣ የሰንደቅ ዓላማን ታሪካዊ አስተዋጽኦና ሀገራዊ ፋይዳ በማስገንዘብ የዜጎችን የሀገር ፍቅር፣ የአንድነትና የመተሳሰብ እሴቶች ለማጠናከር በሚያስችሉ በተለያዩ ሁነቶች ቀኑን እያከበረ ነው። የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ስንታየሁ ደስታ በውይይቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር እንደተናገሩት፣ ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ምልክት፣ የሕዝቦች የጋራ ታሪክና የሀገራዊ አንድነት መገለጫ ነው ብለው ለሰንደቅ ዓላማ ክብር ሁላችንም በአንድነት መቆም አለብን ሲሉ ገልፀዋል። አባቶቻችን ሀገርን ለማፅናትና ነፃነቷን ለማስጠበቅ የከፈሉትን ዋጋ የዛሬው ትውልድ በማስቀጠል ለቀጣዩ ትውልድ በክብር ሊያስረክብ ይገባል ብለዋል አቶ ስንታየሁ። እኛ ኢትዮጲያዊያን የተለያዩ ማንነቶች፣ሀይማኖቶችና ባህሎች ያሉን ቢሆንም፣ ብዝሃነታችንን እንደ ጥንካሬ በመጠቀም እና አንድነታችንን በማፅናት የሀገራችንን የብልፅግና ጉዞ ማረጋገጥ አለብን ብለዋል ዋና ስራ አስፈፃሚው። አባቶቻችን በትጋትና በመስዋዕትነት ያስረከቡንን ሀገር በመጠበቅና የራሳችንን ኃላፊነት በመወጣት ለነገው ትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ዜጋ ግዴታ መሆኑንም ገልፀዋል። የልደታ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ዘሪሁን ሽፈርዳ እንደተናገሩት፣ ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ነፃነት፣ የሉዓላዊነትና የህብረ ብሔራዊ አንድነት ምልክት መሆኑን ገልጸው፣ ይህንን የሀገር መገለጫ ትውልዱ በክብር እንዲጠብቀውና እንዲያከብረው ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። ሰንደቅ ዓላማችን የጋራ መለያችን በመሆኑ በዙሪያው በመሰባሰብ የሀገር ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ፅናትንና መተሳሰብን ማጠናከር እንደሚገባም ክቡር አቶ ዘሪሁን ተናግረዋል። ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት የሥራ መስክ ውጤታማ በመሆን ለሀገራዊ አንድነት፣ ለልማትና ለብልፅግና አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት ብለዋል አቶ ዘሪሁን። የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን ከሰንደቅ ዓላማ ክብር በተጨማሪ የሀገር ፍቅርን፣ የዜጎችን የጋራ ኃላፊነትና የብሔራዊ መግባባት እሴቶችን ለማጠናከር ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑንም አቶ ዘሪሁን ተናግረዋል።

መልዕክትዎን ይላኩ

ሌሎች ዜናዎች